Monday, June 11, 2012

ይህንን ታሪክ የምትነግረን የአንድ ትልቅ ድርጅት መሪ ናት፡፡
«ልጅ እያለሁ እናቴ ከእኔ በአምስት ዓመት የምታንሰዋን ታናሿን እኅቴን ሁልጊዜ «እወድሻለሁ´ ስትላት እሰማ ነበር፡፡ እኔን ግን አልፎ አልፎ ካልሆነ በቀር እንደርሷ አዘውትራ «እወድሻለሁ» አትለኝም፡፡ እርሷ አልቃሻና ነጭናጫ ልጅ ነበረች፡፡ እኔም አልፎ አልፎ ታናሿን እኅቴን እንድከታተላትና እንድጠብቃት ትነግረኝ ነበር፡፡ ይህ ሁኔታ እናቴ እኔን አትወደኝም እንድል አደረገኝ፡፡ ስለዚህም «ቶሎ ቶሎ ተምሬ ወደ ኮሌጅ መግባት አለብኝ፡፡ ከማትወደኝ እናቴ ጋር ለምን እቀመጣለሁ» እል ነበር፡፡

«እንዳልኩትም ጠንክሬ ተምሬ ኮሌጅ ገባሁ፡፡ ኮሌጅ በመጀመርያ ሴሚስተር ላይ ቤቴ በጣም ይናፍቀኝ ነበር፡፡ በተለይ አባቴን ማግኘት እጅግ በጣም እፈልግ ነበር፡፡ እርሱ ለትምህርት ቤት የሚያስፈልገኝን ነገር ሁሉ ይልክልኝ ነበር፡፡ ናፍቆቱ ሲብስብኝ ግን «መምጣት እፈልጋለሁና የአውሮፕላን ትኬት ላክልኝ» አልኩት፡፡ እርሱም «አሁን ገንዘብ የለኝም፤ ሴሚስተሩ ሲያልቅ በዕረፍት ጊዜ ትመጫለሽ» አለኝ፡፡
«ከፋኝ፡፡ አባቴም እንደ እናቴ አይወደኝም ማለት ነው አልኩ፡፡ ቢወደኝ ኖሮማ እርሱ ሲናፍቀኝ ለምን ትኬት አይልክልኝም ነበር፡፡ በቃ በዚያ ቤት ውስጥ እኔን የሚወድ ስለሌለ ወደዚያ ቤት መሄድ የለብኝም ብዬ ወገቤን አሥሬ ተማርኩና ኮሌጅ ጨረስኩ፡፡ የመጀመርያ፣ ሁለተኛና የፒኤች ዲግሪዎቼን እያከታተልኩ በእልህ ተማርኩ፡፡
«አልፎ አልፎ ብቻ ወደ ወላጆቼ ዘንድ ስልክ እደውል ነበር፡፡ የማይወዱኝ ሰዎች ጋር ለገናም ሆነ ለመታሰቢያ ቀን ዝግ መሄድ አልፈልግም ነበር፡፡
«አንድ ቀን አንድ ጓደኛዬ «ላንድ ማርክ» የሚባል ኮርስ እየተሰጠ መሆኑን፣ እርሷም እየተማረች መሆኑን ነገረችኝ፡፡ ስለ ኮርሱ የሚያስረዱ ወረቀቶችንም አመጣችልኝ፡፡ ወረቀቶቹን ሳነባቸው ደስ የሚሉ ነጥቦች ስላገኘሁ ከፍዬ ተመዘገብኩ፡፡
«በኮርሱ ውስጥ «ሕይወትን መልካም ማድረግ» የሚል ክፍል ነበር፡፡ እንዴት አድርገን ነው ሕይወታችንን መልካም የምናደርገው? የትናንት ገጠመኛችንና ልምዳችን በዛሬውና በነገው ሕይወታችን ላይ ምን ዓይነት ተጽዕኖ ያመጣል? ውሳኔዎቻችን ከየት ይመነጫሉ? ውሳኔዎቻችን ሁሉ ትክክል ናቸው ወይ? የተመሠረቱትስ በእውነታ ላይ ነው ወይ? እያለ ይተነትናል፡፡
«ክፍለ ትምህርቱ ሊጠናቀቅ ሲል መምህሩ በሕይወት ደስተኛ ለመሆን ከሚያስፈልጉን ነገሮች መካከል ሁለቱ ወሳኝ ናቸው አሉ፡፡ ይቅርታ መጠየቅና ይቅር ማለት፡፡ ይቅርታ የሚጠየቀውን ሰው ሳይሆን የሚጠይቀውን ሰው ይጠቅመዋል፡፡ በደል ሸክም ነው፤ ፀፀትም ሕመም ነው፡፡ ይቅርታ መጠየቅ ሸክምን ማራገፍና ሕመምን መፈወስ ነው፡፡ በደል ኅሊናን ያበላሻል፤ ውሳኔዎቻችንን ያበላሻል፡፡ አመለካከታችንን ያበላሻል፡፡ ስለ ሰው ያለንን እምነት ያበላሻል፡፡ ዘወትር የማይለቅ የቤት ሥራም ይሰጣል፡፡
«በደል ያለበት ሰው ሳይዘጋ መብራቱን ያጠፋ ኮምፒውተር ማለት ነው፡፡ ከላይ ሲያዩት ኮምፒውተሩ ሥራ ጨርሶ ያረፈ ይመስላል፡፡ በውስጡ ግን በሥራ የተጠመደ «ቢዚ» ነው፡፡ በደል ያለበት ሰው፣ የተቀየመም ሰው፣ በሰው ያዘነና ያኮረፈም ሰው ዕረፍት ያገኘ ይመስለው ይሆናል እንጂ ነፍሱ ግን «ቢዚ» ናት፡፡ በውስጧ የገባው ቫይረስ በማያስፈልጉ ሥራዎች ጠምዷታል፡፡ ለብዙ ነገር ልታውለው የነበረውን ችሎታና ጊዜ፤ ልብና አእምሮ፣ ነገር ለማብሰልሰልና ሁል ጊዜ ወደ ኋላ ለመጓዝ እንድታውለው አድርጓታል፡፡ በደል ያለበት ሰው ወደፊት ለመጓዝ ያዳግተዋል፡፡ አዘውትሮም ባሳለፈው ሕይወት ይጠመዳል፡፡ እያሉ መምህሩ አብራሩ፡፡
«ከዚያም አንድ የክፍል ሥራ ሰጡን፡፡ ቀጣዩን ክፍለ ጊዜ ከመጀመራችን በፊት አርባ ደቂቃ አለን፡፡ በዚህ አርባ ደቂቃ በሕይወታችሁ ያሳዘኑዋችሁ ሦስት ሰዎች ጋር ደውላችሁ እናንተ ይቅርታ ጠይቋቸው፡፡ ከዚያ ያጋጠማችሁን ነገር በቀጣዩ ክፍለ ጊዜ ከአርባ ደቂቃ በኋላ ትነግሩኛላችሁ፡፡ ክፍለ ጊዜው አበቃ፡፡
«እኔ መጀመርያ የደወልኩት እናቴ ጋር ነው፡፡ «እናቴ ይቅርታ ላለፉት አሥራ አምስት ዓመታት ተቀይሜሽ ነበር» አልኳት፡፡ «ለምን አለችኝ፡፡ ተገርማም፤ ደንግጣም፡፡ «ስለማትወጅኝ» አልኳት፡፡ «በምን ዐወቅሽ አለችኝ፡፡ «ታናሿን እኅቴን እንጂ እኔን እወድሻለሁ ብለሽኝ አታውቂም» አልኳት፡፡ «ታናሽ እኅትሽኮ ሕመምተኛ ናት፡፡ የተለየ ጥንቃቄ ያስፈልጋት ነበር፡፡ ሕመሟ እያበሳጫት ትነጫነጭ ነበር፡፡ ስለዚህ ሁልጊዜ እንደምወዳት ማወቅ ነበረባት፡፡ እንቺንኮ አምስት ዓመት ለብቻሽ አሳድጌሻለሁ፡፡ ጤነኛ ነበርሽ፡፡ አንቺ በሰላም እንድትማሪ፣ አባትሸም በሰላም እንዲሠራ እኔ እኅትሽን መከባከብ ነበረብኝ፡፡ አንቺ እንደ እርሷ ዓይነት ልጅ ቢኖርሽ ኖሮ ምን ታደርጊ ነበር ይህ ለእኔ አስቤው የማላውቅ ታሪክና አስቤው የማላውቅ ጥያቄ ነበር፡፡
«እውነቷን ነው፤ ታናሿ እኅቴ ስትወለድ ጀምራ ሕመምተኛ ነበረች፡፡ ማልቀስና መነጫነጭ የዘወትር ተግባሯ ነበር፡፡ እናቴ ምንጊዜም እርሷን ይዛ ታችኛው ቤት ትወርድ ነበር፡፡ አባቴ ለረዥም ሰዓት ስለሚሠራ ቤት ሲመጣ ዕረፍት ይፈልግ ነበር፡፡ የታናሿ እኅቴ ልቅሶ ደግሞ ይረብሸዋል፡፡ የተወሰነ ጊዜ ከእርሷ ጋር ካሳለፈ በኋላ ለቀጣዩ ሥራ ዕረፍት ለማግኘት ይተኛ ነበር፡፡ እውነትም እናቴ እኅቴን ባትከታተላት ኖሮ እኔ አልማርም ነበር፡፡ እኔ እኅቴን የምከታተለው እናቴ ገበያ ስትሄድና ምግብ ስትሠራልን ብቻ ነበር፡፡ ሌሊት እንኳን ዕረፍት አልነበራትም፡፡ ለካ ይሄ ሁሉ ለእኔ በነበራት ፍቅር ነበር፡፡ ለምን ግን ቀደም ብዬ ይህንን ማሰብ አልቻልኩም? አለቀስኩ፡፡ በስልክ እየሰማችኝ ስቅስቅ ብዬ አለቀስኩ፡፡ «እና እናቴ እኔን ትወጅኝ ነበር» አልኳት በድጋሚ፡፡ «በርግጥ፣ ምን ጥርጥር አለው፤ አንቺኮ የመጀመርያ ልጄ ነሽ» አለቀስኩ፡፡
«ቀጥዬ ወደ አባቴ ነበር የደወልኩት፡፡ «አባዬ ተቀይሜህ ነበርና ይቅርታ» አልኩት፡፡ ግራ ገብቶት «ለምን አለኝ?» «ስለማትወደኝ» አልኩት፡፡ እርሱም እንደናቴ «በምን ዐወቅሽ ነበር ያለኝ፡፡ «ያኔ ናፍቀህኝ ልመጣ ነውና ትኬት ላክልኝ ስልህ እምቢ አልክ፡፡ ብትወደኝ ኖሮ ትልክልኝ ነበር» አልኩት፡፡
«እኔ መላክ አቅቶኝ አልነበረም፡፡ ከዚያ በላይ የሆነ ገንዘብ ለትምህርት ቤትሽና ለትምህርት መሣርያሽ እየከፈልኩልሽ ነበርኮ፡፡ ባልወድሽ ለምን እንደሌሎቹ ሠርተሽ ተማሪ አላልኩሽም? ለረዥም ሰዓት የምሠራውኮ የአንቺን ትምህርት ቤት ለመክፈል ነበር፡፡ ያን ጊዜ ግን አንቺ በእኔ ናፍቆት ምክንያት ከመጣሽ አትመለሽም ብዬ አሰብኩ፡፡ ካልተመለሽ ደግሞ ከትምህርትሽ ትስተጓጎያለሽ፡፡ ከንቱ ልጅ ሆነሽም ትቀሪያለሽ፡፡ ናፍቆቱ ያልፍልሻል፡፡ በትምህርት ግን ቀልድ የለም፡፡ ስለዚህ አልላክሁልሽም፡፡ እኔ መቼም እወድሻለሁ፡፡» ስሰማው አለቅስ ነበር፡፡ ልቅሶዬንም ዕንባዬንም መቆጣጠር አቅቶኝ ነበር፡፡
«እነዚህ ሁለቱ ገጠመኞቼ አንድ ነገር አስተማሩኝ፡፡ ለስሕተት ስለሚዳርጉን ሦስት ምዕራፎች፡፡ በሕይወት ጉዟችን፡፡ ለስሕተት የሚዳርጉን ሦስት ምዕራች አሉ፡፡ የሚመስሉን ነገሮች፣ የምንፈጥራቸው ታሪኮችና በፈጠርናቸው ታሪኮች ላይ ተመሥርተን የምንወስናቸው ውሳኔዎች፡፡
«አንዳንዴ በኑሯችን የምናያቸው የምንሰማቸውና የምንገምታቸው ነገሮች አሉ፡፡ ለእኛ የሚመስሉን፡፡ ልክ እኔ እናቴ ለእኅቴ የምትላትን፣ አባቴም ትኬት አልልክም ያለውን አጋጣሚ እንደተጠቀምኩበት ማለት ነው፡፡ ሰው ያንን ያለበት፣ ያደረገበት፣ ወይም ያላደረገበት ምክንያት እኛ ካሰብነው ውጭ ሊሆን ይችላል፡፡ እኛ መሰለን እንጂ ሰውዬው እንደዚያ ማለቱም ላይሆን ይችላል፡፡ የምናየው ነገር እኛ ተርጉመን ተረድተነው እንጂ እንደተረዳነው ላይሆንም ይችላል፡፡
«ይኼ የመጀመርያው ነገር ነው፡፡ ነገር ግን ብቻውን አይቀርም፡፡ በዚህ የተሳሳተ ገጠመኝ ላይ እንነሣና የየራሳችንን ታሪኮች እንፈጥራለን፡፡ እናቴ እኔን እንደ እኅቴ አዘውትራ «እወድሻለሁ» የማትለኝ ስለማትወደኝ ነው ያልኩት የራሴ ፈጠራ ነበር፡፡ እናንተም እንዲሁ ትፈጥሩ ይሆናል፡፡ እንዲህ ማለቱ ነው፣ እንዲያ ማለቷ ነው፡፡ የተወችኝ በዚህ ምክንያት ነው፤ ያልጋበዘኝ እንዲህ አስቦኝ ነው፡፡ ሰላም ያላለኝ ለዚህ ወይንም ለዚያ ምክንያት ነው፡፡ ሰሞኑን የጠፋው፣ ያልደወለልኝ፤ ያላስተዛዘነኝ በዚህና በዚያ ምክንያት ነው እያልን የየራሳችንን ታሪኮች እንሠራለን፡፡ ለእነዚያ ታሪኮች ደግሞ ካለፉት ልምዶቻችን እየተነሣን እጅና እግር፣ ዓይንና ጆሮ፣ ፀጉርና ምላስ እናበጅላቸዋለን፡፡ ለብዙ ጊዜ በታሪኮቹ ላይ ከማሰባችንና ከመገጣጠማችን የተነሣም እውነተኛ ታሪኮች መስለው ይወጣሉ፡፡ በደንብ የተዘጋጀ የፊልም ረቂቅ ወይንም ባለሞያ የደረሰው ድርሰት ይመስላሉ፡፡ ትረካ እናበጅላቸዋለን፡፡
«እነርሱም በራሳቸው አያቆሙም፡፡ በእነዚህ የተሳሳቱ ታሪኮች ላይ እንነሣና ውሳኔ እንወስናለን፡፡ በቃ ከዛሬ ጀምሮ እለየዋለሁ፣ አልደውልለትም፣ እፈታዋለሁ፣ ስልኩን አላነሣም፣ ወዳጅነቴን አቆማለሁ፣ ወደ እርሱ ዘንድ አልሄድም፤ እንዲህና እንዲያ ብዬ እመልስለታለሁ፤ እንዲህ ወይም እንዲያ ዓይነት ርምጃ እወስዳለሁ እንላለን፡፡ በዚያ ውሳኔ መሠረትም እንኖራለን፡፡
«ሰውዬው እኛ እዚህ ደረጃ መድረሳችንን አያውቅም፡፡ ለኛ እርሱ የተቀየረ መስሎናል፡፡ የሚገርማችሁ ግን የተቀየርነው እኛ ነን፡፡ በፈጠርነው መረጃ፣ በሠራነው ታሪክ፣ በመጨረሻም በወሰንነው ውሳኔ የተነሣ ሳናውቀው እኛ ራሳችን ተቀይረን ሰውዬው የተቀየረ ይመስለናል፡፡ ዓይናችን ስለተቀየረ የድሮውን አናየውም፤ ጆሯችንም ስለተቀየረ የድሮውን አንሰማውም፤ ልቡናችን ስለተቀየረም እንደ ድሮው አድርገን አንረዳውም፡፡ ስለዚህ እገሌ ተቀየረብን እንላለን፡፡ አንዳንዴም እጅግ ብዙዎች የተቀየሩብንም ይመስለናል፡፡
ዘጉኝ፣ አገለሉኝ፣ ናቁኝ፣ አሾፉብኝ፣ ተጠቃቀሱብኝ፣ አሙኝ፣ ተመካከሩብኝ፣ አደሙብኝ እያልን እኛው ራሳችን ራሳችንን አግልለን አግልለን ሌላ ደረጃ ላይ እንደርሳለን፡፡ እኛው እንሸሻለን፣ እኛው እንጠፋለን፣ እኛው እንለያለን፡፡ አሁንም ግን ሌሎች ያደረጉት ነው የሚመስለን፡፡
[እኔ እዚህ ላይ ሰይጣን ትዝ አለኝ፤ ከሰማያት ሲወድቅ እርሱ ወደ እንጦሮጦስ ሲወርድ «ሥላሴ ፈርተውኝ ሸሹ» ይል ነበር ብለው አበው ነግረውናል፡፡ እርሱ መሸሹን አያውቀውም ነበር፡፡]
«ስለዚህ እስኪ ለይቅርታ በር እንክፈት፡፡ ሰዎችን ብቻ ሳይሆን ታሪክንም ይቅር እንበለው፡፡ ምናልባት አንዳንድ በሕይወታችን የወሰንናቸው ውሳኔዎች መጀመርያም በተሳሳቱ መረጃዎች፣ ከዚያም በተፈጠሩ ታሪኮች የወሰንናቸው ሊሆኑ ይችላሉና፡፡ ምናልባት እኛ ከፊሉን የብርጭቆ ውኃ ከማየት ይልቅ ባዶውን የብርጭቆውን ክፍል አይተን ይሆናል፡፡ ያን ጊዜ ውኃውን የቀዳው ሰው ውኃ ማድረጉን ያያል፤ ውኃውን የተቀበለው ሰው ደግሞ ከውኃው መወሰዱን ያያል፡፡ ይኼኛው ተደረገ ሲል፣ ያኛው ተወሰደ ይላል፡፡ ሁለቱም ለምን? ይሉና የየራሳቸውን ታሪክ ይፈጥራሉ፡፡ የየራሳቸውንም ውሳኔ ይወስናሉ፡፡
«አሁንም ይህንን ትምህርት ላስተምራችሁ የመጣሁት ከእኔ እንድትማሩ ነው፡፡ ይህንን ክፍለ ጊዜ ስንጨርስ ደውሉና በሕይወታችሁ ያሳዘኗችሁን፣ ያስቀየሟችሁን ወይም ያስኮረፏችሁን ሦስት ሰዎች ይቅርታ ጠይቁ፡፡ ወይንም በሕይወታችሁ ያዘናችሁበትንና የተጎዳችሁበትን ታሪክ ይቅር በሉት፡፡ ምናልባት እኔ ካገኘሁት ርካታ፣ ሰላምና ትምህርት የበለጠ ታገኙ ይሆናል፡፡ መቀበል የመስጠትን ያህል፣ መብላት የማብላትን ያህል፣ መጠጣት የማጠጣትን ያህል፣ መልበስ የማልበስን ያህል አያስደትስም፡፡ ይህንን ደግሞ ስትመለሱ ትነግሩኛላችሁ፡፡ ክፍለ ጊዜው ሲያልቅ ሁሉም ወደየ ስልኩ ሮጠ፡፡
ሳንሆዜ፣ ካሊፎርንያ
© ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ የወጣ በመሆኑ በተመሳሳይ ኅትመት ላይ ባታውሉትይመረጣል፡

0 comments:

Post a Comment