Monday, June 11, 2012

የቅዱስ ሲኖዶስ ዐሥረኛ ቀን የቀትር በኋላ ውሎ(የደጀ ሰላም ዘገባ)

·         ቅዱስ ሲኖዶስ በውሳኔው መግለጫ ዝግጅት ላይ ጥንቃቄ አድርጓል፤ በመላው ዓለምየሚሠራጨውን መግለጫ በጽሑፍ የሚያዘጋጁት ከምልአተ ጉባኤው የተመረጡ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ናቸው።
·      አባ ሰረቀ በተጠየቁበት ጉዳይ እምነታቸውን በጽሑፍ ይገልጣሉ፤ ለ”እውነትና ንጋት” ሌላ ማስተባበያ መጽሐፍ እንዲጽፉ ተወስኗል።
·        ሊቀ ካህናት ጌታቸው ዶኒ ለፕሮቴስንታንት ቤተ እምነት የጻፉት ደብዳቤ የእርሳቸው ላለመኾኑ በጽሑፍ ያረጋግጣሉ።
·        በጋሻው ደሳለኝ ተጨማሪ ስሕተቶቹ ተመርምረውና ራሱም ተጠይቆ የውሳኔ ሐሳብ እንዲቀርብ ተወስኗል።

·         ሊቃውንት ጉባኤው በቤተ ክርስቲያናችን ላይ የሚነሡ ማንኛውንም የሃይማኖት፣ የሥርዐትና የታሪክ ጥያቄዎች ለመመለስ በሚያስችል የሰው ኀይልና በልዩ በጀት እንዲጠናከር ተወስኗል።
 (ደጀ ሰላም፤ ግንቦት 15/2004 ዓ.ም፤ May 23/ 2012)፦ የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በትናንት፣ ግንቦት 15 ቀን 2004 ዓ.ም የቀትር በኋላ ውሎው በቅዱስ ሲኖዶስ የተሠየመው የብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትና የሊቃውንት ጉባኤ አባላት ጥምር ኮሚቴ በሐሰተኛ ትምህርታቸው ሊወገዙና ሊለዩ ይገባቸዋል ባላቸው የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ አራማጅ ግለሰቦች ላይ ያቀረበውን ጥናታዊ መግለጫና የውሳኔ ሐሳብ መርምሮ አጸደቀ፡፡
በምልአተ ጉባኤው ውሳኔ መሠረት ግለሰቦቹ በቀረቡባቸው ማስረጃዎች የለየላቸው መናፍቃን መኾናቸውን የተረጋገጠ በመኾኑ ውግዘት ይተላለፍባቸዋል፤ የቤተ ክርስቲያንን ክብር በመዳፈራቸው በሕግ ይጠየቃሉ፤ በቤተ ክርስቲያን የዜና አውታሮችም ማንነታቸው ተጠቅሶ በሐሰተኛ ትምህርታቸው ተወግዘው የተለዩ ለመኾናቸው ለምእመናን መግለጫ ይወጣባቸዋል፡፡
በዚህም መሠረት፡-
1)    ጽጌ ስጦታው፡- ይህ ግለሰብ በ1995 ዓ.ም ሚያዝያ ወር ለቅዱስ ሲኖዶስ ባስገባው የይቅርታ ይደረግልኝ ደብዳቤ “ያስተማርኹት፣ የተናገርኹትና የጻፍኹት ሁሉ ስሕተት መኾኑን ስላመንኹ ይህን ሁሉ ስሕተቴን ቅዱስ ሲኖዶስ ተረድቶልኝ ይቅርታ እንዲያደርግልኝና ትምህርቱን እንድማር ይፈቀድልኝ ዘንድ በታላቅ ትሕትና አመለክታለኹ” የሚል ነበር፡፡ በዚህም መሠረት ንስሐ እንዲገባ ተመክሮ ነበር፤ ነገር ግን ምክሩን ሊጠቀምበት እንዳልቻለ ታውቋል፡፡ ይህ ግለሰብ በተደጋጋሚ ተመክሮ ያልተመለሰ የለየለት መናፍቅ ኾኖ ከቤተ ክርስቲያን የወጣና የተለየ መኾኑ የተረጋገጠ ነው፡፡ በመኾኑም ውግዘት እንዲተላለፍበትና ይኸውም በሁሉ የቤተ ክርስቲያኒቱ የዜና አውታሮች ለምእመናን እንዲገለጽ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡
2)   መጋቤ ጥበብ ሰሎሞን መኰንን፡- “ኦርቶዶክሳዊነት እንዲህ ነው!” (1999 ዓ.ም) እና “በውኑ በማርያም ማመን ይገባሃልን?” በሚሉ ርእሶች ባሳተማቸው ክሕደትና ኑፋቄ የመላባቸው መጽሐፎቹ የክርስቶስን አምላክነት የሚክድ፣ የእመቤታችንን ንጽሕና፣ ቅድስናና አማላጅነት የሚቃወምና የሚነቅፍ በአጠቃላይ የቤተ ክርስቲያናችንን አስተምህሮ የሚያፋልሱ መኾኑ ስለተረጋገጠ ጸሐፊውም ኾነ መጽሐፉ ሊወገዙ እንደሚገባ ቅዱስ ሲኖዶስ አምኖበታል፡፡ በመኾኑም ይህ አሳሳች ሐሳብ ምእመናንን እንዳያደናግር የቅዱስ ሲኖዶስ ቀኖናዊ ውሳኔ በቤተ ክርስቲያናችን የዜና አውታሮች ለምእመናን እንዲገለጽ ተወስኗል፡፡
3)   ዲያቆን ደረጀ ገዙ ከኑፋቄ ጓደኛው በዛ ሰፈርህ ጋራ የኑፋቄ ትምህርት ያስተማረና “መቅደስ የገቡ መናፍቃን” በሚል ርእስ የኑፋቄ መጽሐፍ ያሳተመ ነው፡፡ በባሕር ዳር እና አዲስ አበባ ከተሞች የአስተማረው ትምህርት ኑፋቄ የተመላበት እንደ ኾነ የቀረበበት ማስረጃ ያረጋግጣል፡፡ የበዛ ሰፈርህ የኑፋቄ ትምህርትም ከዲያቆን ደረጀ ገዙ ጋራ አንድ ነው፡፡ በመኾኑም በቀረበው ማስረጃ ተራ ቁጥር (3) እና (4) የተገለጹት እኒህ ሁለት ግለሰቦች በማስረጃ ተደግፎ በቀረበው የሐሰት ትምህርታቸው ተወግዘው እንዲለዩ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡ ይኸው የቅዱስ ሲኖዶስ ቀኖናዊ አቋም በቤተ ክርስቲያን የዜና አውታሮች ለምእመናን እንዲገለጽም ትእዛዝ ሰጥቷል፡፡
4)   አግዛቸው ተፈራ እና ሁለት ግለሰቦች፡- ይህ ግለሰብ በአሰላ ከተማ ደብረ መድኃኒት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ት/ቤት ሲያገለግል የኑፋቄ ትምህርት በማስተማሩ በሰንበት ት/ቤቱ አባላት ክትትልና በሰበካ ጉባኤው ጥንካሬ ማንነቱ ተጋልጦ አልመለስ ሲል ከአገልግሎቱ የታገደ ነው፡፡ ከሚወገዙት የመናፍቃን ድርጅቶች አንዱ የ‹ማኅበረ በኵር› በኾነው ‹ጮራ› መጽሔት በዋና አዘጋጅነት ተቀጥሮ እየሠራ የሚገኘው ግለሰቡ “የለውጥ ያለህ” (2001 ዓ.ም) ፣ “የተቀበረ መክሊት” (1993 ዓ.ም) እና “አልተሳሳትንም” (2003 ዓ.ም) በሚሉ ርእሶች ባሳተማቸው ክሕደትና ኑፋቄ የተመላባቸው መጽሐፎቹ “ቤተ ክርስቲያን ኢ-መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮዎች ስላሏት የአስተምህሮ ለውጥ ያስፈልጋታል፤ በእንግዳ ትምህርቶችና የፈጠራ ድርሰቶች ነው የምትመራው፤” ሲል ጽፏል፡፡

ዲያቆን አግዛቸው ተፈራ ÷ አቶ አሰፋ ተገኝ እና አቶ ብሥራት ጌታቸው ከሚባሉ ሌሎች ሁለት ግለሰቦች ጋራ በመፈጸሙት የመናፍቅነት ተግባር የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል፣ የአምስት አድባራት የሰበካ ጉባኤ አባላትና ካህናት በተገኙበት ሰኔ 4 ቀን 1991 ዓ.ም ቀርበው እንዲጠየቁ ከተደረገ በኋላ ከስሕተታቸው የማይመለሱ መኾናቸው በመረጋገጡ በማንኛውም መንፈሳዊ ተግባር እንዳይሳተፉ መታገዳቸውን ቅዱስ ሲኖዶስ በቀረበለት ማስረጃ አረጋግጧል፡፡ በመኾኑም ቅዱስ ሲኖዶሱ በአግዛቸው ተፈራና ሁለቱ ግለሰቦች ላይ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል የወሰዱባቸውን ቀኖናዊ ውሳኔ አጽንቷል፤ ይኸው ቀኖናዊ ውሳኔም በቤተ ክርስቲያኒቱ ብዙኀን መገናኛ ለምእመናን እንዲገለጽ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡

በጋሻው ደሳለኝን በተመለከተ ርእሰ መንበሩ አቡነ ጳውሎስ በግለሰቡ የተጻፈ ነው የተባለውን ደብዳቤ ለምልአተ ጉባኤው በንባብ አሰምተዋል፡፡ ፓትርያርኩ ከእጅጋየሁ በየነና ሌሎች የጨለማው ቡድን አባላት ጋራ ሳይመክሩበት እንዳልቀረ የተገመተው የበጋሻው ደብዳቤ ÷ እርሱ ከሚጠየቅበት ጉዳይ ንጹሕ መኾኑንና “ከሳሼ ማኅበረ ቅዱሳን እንጂ ቤተ ክርስቲያን አይደለችም” የሚል ነው፡፡

የሃይማኖት ሕጸጽ ጥቆማ የቀረበባቸውን ግለሰቦች ጉዳይ ባጣራው ጥምር ኮሚቴ በተደጋጋሚ ለጥያቄ ተፈልጎ ያልቀረበው በጋሻው በእጅጋየሁ በየነ ተበረታቶ በፓትርያርኩ ተተግኖ ያቀረበው ጥያቄ ግን በምልአተ ጉባኤው ዘንድ ተቀባይነት አላገኘም፡፡ ይልቁንም ጥምር ኮሚቴው በጋሻው ኤሽታኦል” (2001 ዓ.ም) በተሰኘው መጽሐፉ በዐላዋቂ ድፍረትና ጥንቃቄ በሚጎድላቸው ንግግሮቹ የተናገረውን ማስረጃ በመቀበል በቤተ ክርስቲያናችን ያልተለመደና ከቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ ውጭ የኾነ ፍጹም ስሕተት መኾኑን አረጋግጧል፡፡

ምልአተ ጉባኤው ግን በዚህ ብቻ ሳይወሰን ሌሎች የበጋሻው ዐበይት ሕጸጾች የሚገኙባቸው መጽሐፎቹና ሲዲዎቹ ለምን ተጨምረው እንዳልተመረመሩ ጠይቋል፤ ይህ ጥያቄ በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ኮሚቴ አባል የኾኑት ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ ሳይቀሩ ያነሡት ነበር፡፡ ለጥያቄው የተሰጠው ምላሽ የካሴት ወይም ቪሲዲ ማስረጃዎች ተመሳስለው ለሚሠሩ የተጭበረበሩ ይዘቶች የተጋለጡ መኾኑንና የባለሞያ እገዛና ሞያዊ ምክር የሚሰጥ አካል እንደሚያስፈልግ የሚያመለክት ነው፡፡ በመኾኑም ቅዱስ ሲኖዶስ በጋሻው ደሳለኝ ለጥያቄ በተደጋጋሚ ተጠርቶ አለመገኘቱን ከግምት በማስገባት፣ በምሳሌነት የቀረበውን “በራስ ቅል ኮረብታ ክርስቶስና ዲያብሎስ ቁማር ተጫወቱ. . .” የሚለውን የድፍረት  ንግግሩን እንደ መነሻ በመውሰድ ሌሎች ካሴቶቹ ወይም ሲዲዎቹ (ከዘጠኝ ያላነሱ እንደሚኾኑ ተገምቷል) በአግባቡ እንዲመረመሩ ወስኗል፡፡ ግለሰቡ ወደፊት ቀርቦ እንዲጠየቅና በሚሰጠው መልስ ጉዳዩ እንዲታይ ጥምር ኮሚቴው በሪፖርቱ ያስቀመጠውን አስተያየት ቅዱስ ሲኖዶስ በመቀበል በጋሻው ተጠርቶና ተጠይቆ ከውሳኔ ሐሳብ ጋራ ለጥቅምት ቅዱስ ሲኖዶሰ ምልአተ ጉባኤ የውሳኔ ሐሳብ እንዲቀርብለት ትእዛዝ ሰጥቷል፡፡

ከበጋሻው ቀደም ሲል ከተጠቀሰው በተጨማሪ “ነሁሽታን” በተባለው ሲዲው÷ “ድነናልኮ እኛ፤ ጠበል ያድነናል፤ መስቀል ያድነናል፤ የኾነ ነገር ያድነናል አትበል”፤ “ሴትዮዋ ገብርኤልን አትግፋኝ አለችው” እያለ ይዘባርቃል፡፡ “ጠላቶችህ ዋሹብኽ” በተሰኘው የስብከት ሲዲው÷ “እግዚአብሔር ቆራሌ ሰብሳቢ ነው”፤ “ጌታ መከራው እየመጣ እያለ ወደ ጌቴ ሰማኒ ሄደና ቅልጥ አድርጎ ከሐዋርያት ጋራ ይዘምራል፤” “ራዕያችን በጨረቃ ላይ ቤተ መቅደስ መሥራት ነው”፤ “ለካ ትወዱናላችኹ፤ ታከብሩናላችኹ፤ እኛ ቀለል አድርገን ነበር የምናገለግለው፤. . . ለካ ይህ ሁሉ ሕዝብ በእኛ ላይ ተደግፏል፤ እኛ ብንወድቅ ለካ ይህ ሁሉ ሕዝብ ይወድቅ ነበር፤ እኛ ብንሸነፍ ይህ ሁሉ ሕዝብ ይሸነፍ ነበር፤. . . ይህ መስቀል የማያመጣው ጣጣ የለም”“የመማጸኛ ከተማ” በተሰኘው ደግሞ “ከጌታ ጨርቅ ይልቅ እመቤታችን አትበልጥም”፤ በሉቃ.8÷43 ላይ የሚገኘውን ታሪክ በመጥቀስ “ደም ሲፈሳት የነበረችው ሴት በጌታ ጨርቅ አምና ዳነች፤ እርሷ በእናቱ አይደለም፤ በአባቱም አይደለም በእርሱ ጨርቅ አመነች” በማለት ይዘባርቃል፡፡

በተለያየ ቦታ ባሰማቸው ስብከቶቹም “ለማርያም ከበሮ አይመታም ለጌታ እንጂ”፤ “ሥላሴ አትበሉ”፤ “ሥላሴ አትበሉ ተባለ እንጂ በሥላሴ አትመኑ አልተባለም”፤ “ቅዱስ ጳውሎስ ፋሲካችን እርሱ ነው አለ፤ ማን ነው እርሱ - ኢየሱስ ክርስቶስ፤ እግዚአብሔርና ኢየሱስ ክርስቶስ የሚለውን አትቀላቅሉ እባካችኹ፤ የምናስተምርም ሰዎች ለይተን እናስተምራቸው፤ ኢየሱስ የሚለውን ስም ሽሽት እግዚአብሔር፣ ሥላሴ፣ ወደዚህ ወደዚያ አትበሉ”፤ “በዕድር ደንብ ነው ያለው እስከ አሁን፣ የወንጌል ሕግ አልገባውም፤ የንፍሮ ቀቃይ ልጅ. . .” የሚሉት ጥንቃቄ በጎደላቸውና ድፍረት በተመላባቸው ንግግሮቹ ብዙዎችን አሳስቷል፡፡

በመኾኑም በጋሻው በዐላዋቂ ድፍረት ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን በመጣስ ለተናገራቸው ገና በጥምር ኮሚቴው ፊት ቀርቦ የሚጠየቅ እንጂ አንዳንድ መፍቀሬ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ብሎጎች በችኮላ እንዳናፈሱት ከሚጠየቅበት ጉዳይ “ነጻ የተባለ ወይም ነጻ የወጣ” አይደለም፡፡
ጥምር ኮሚቴው በአባ ሰረቀ ላይ ያቀረበውን በተመለከተ ባቀረበው ሪፖርት ጥር 18 ቀን 1997 ዓ.ም በዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማቲያስ ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት በጻፉት 12 ገጽ የጽሑፍ መግለጫ ገጽ 5 ላይ “እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከአዳም በዘር የሚተላለፍ የውርስ ኀጢአት (ጥንተ አብሶ) ነበረባት፤” የሚለውን የቀሲስ አስተርኣየ ጽጌን ትምህርት ደግፎ ሰባት አባላት ያሉበት ጉባኤ ባሳለፈው ውሳኔ የአባ ሰረቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤል (ቆሞስ) ስም በስድስተኛ ተራ ቁጥር ተጠቅሶ መገኘቱን የጽሑፍ መግለጫው ያረጋግጣል፡፡

ራሳቸው አባ ሰረቀ “እውነትና ንጋት” በሚል ርእስ ባሳተሙት መጽሐፍ በገጽ 38 ላይ ስለዚሁ ጉዳይ የተገለጸውን ሙሉውን ቃል የሰፈረበትን እትም አሰራጭተዋል፡፡ የወቅቱን የተሐድሶ መናፍቃንና ተዛማጅ ችግሮች አስመልክቶ ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሰንበት ት/ቤቶች በጋራ የሰጠው 41 ገጽ መግለጫ ስም የሌለው የ12 ሰዎች ፊርማ ብቻ ይዞ በቀረበው ጽሑፍ በገጽ 17 ላይ “የተሐድሶ ኑፋቄ አራማጆች እነማን ናቸው?” በማለት በጥያቄ ምልክት ከጠቀሷቸው ሰዎች በሁለተኛው ተራ ቁጥር አባ ሰረቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤል መኾናቸውን ያሳያል፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን ለአጣሪ ኮሚቴው ባቀረበው ሰነድ ላይ አባ ሰረቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤል “ከአጽራረ ቤተ ክርስቲያን ጋራ አብረው መሥራታቸውንና አብረው የሚሠሩ በሌላ እምነት ያሉ አስቸጋሪ ሰዎችን” ለማስረጃ ያህል አቅርበዋቸዋል፡፡ እኒህም፡- ሀ) ብርሃኑ አበጋዝ - የታወቀ የተሐድሶ አባል፤ ለ) ሙሉጌታ ወልደ ገብርኤል - በኑፋቄው ከቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የተባረረ የለየለት ፕሮቴስታንት፤ (አሁንም በየድረ ገጹ ላይ የክህደት ጽሑፎቹን በማውጣት ላይ የሚገኝ)፤ ሐ) አባ ኀይለ ሚካኤል ተክለ ሃይማኖት - በሄዱበት ቦታ ሁሉ ችግር የሚፈጥሩና በኑፋቄ የሚታወቁ ግለሰብ በማለት በአባሪ 11 ገጽ ማስረጃ አስደግፈው ለአጣሪ ኮሚቴው አቅርበውታል፡፡

አባ ሰረቀ በእመቤታችን ንጽሕና ላይ አቋማቸው ምን እንደኾነ ወይም ከማን ወገን እንደኾነ ለይተው እንዲያሳውቁ ከሰሜን አሜሪካ ለቅዱስ ሲኖዶስ የተላከው ደብዳቤ ተነቦላቸው እንዲሰሙት ከተደረገ በኋላ ተጠይቀዋል፡፡ 

እርሳቸውም ሲመልሱ፡-
“ስለ ነገረ ማርያም አስተምህሮ በአሜሪካ በቀሲስ አስትርኣየ ጽጌና በማኅበረ ካህናቱ በተደረገው ውይይት በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ እንዲሰጥበት ወደ ኢትዮጵያ መላካችን የታወቀ ነው፡፡ በዚህ ኹኔታ ላይ የእኔ አቋም የቤተ ክርስቲያኔ ቅዱስ ሲኖዶስ የሰጠውና የሚሰጠው ውሳኔ ነው፡፡ ይኸውም “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት፣ ሥርዐተ አምልኮና የውጭ ግንኙነት” በሚል ርእስ ቅዱስ ሲኖዶስ ፈቅዶ በታተመው የቤተ ክርስቲያናችን ትምህርት ስለ ነገረ ማርያም አስተምህሮ የተገለጸው ትምህርት ቀድሞም የማምነው፣ አሁንም የማረጋግጠው እርሱን ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ስለ ነገረ ማርያም አስተምህሮ የተናገርኹት፣ ያስተማርኹትና የጻፍኹት የለም፡፡ በነገረ ማርያም ላይ ያለኝ አቋምና ጽኑዕ እምነት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በወሰነው ውሳኔ ብቻ ነው፤ አምላካችኹ ያየኛል፡፡ ከዚህ የተለየ ዓላማና ተልእኮ የለኝም፡፡” 
በማለት አሁንም ያለውን የእምነት አቋማቸውን ስለ መግለጻቸው የአጣሪ ኮሚቴው ሪፖርት ያብራራል፡፡ ይህን የአባ ሠረቀ ብርሃንን ምስክርነት መሠረት በማድረግ የሪፖርቱ የውሳኔ ሐሳብ አባ ሠረቀ ብርሃን የተጠቀሰው የነገረ ማርያም አስተምህሮ የሚያስጠይቃቸው ኾኖ ያልተገኘ መኾኑን ጉባኤው መገንዘቡን ያስረዳል፡፡ ስለዚህም ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ይሰጥበት ዘንድ የውሳኔ ሐሳቡን አቅርቧል፡፡

የውሳኔ ሐሳቡን ሙሉ በሙሉ የተቀበለው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤም ባለ ሁለት ነጥብ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡ ይኸውም አንደኛ፡- ቆሞስ አባ ሠረቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤል “በነገረ ማርያም ላይ ያለኝ አቋምና ጽኑዕ እምነት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በወሰነው ውሳኔ ብቻ ነው፤” ሲሉ በቃል ለአጣሪ ኮሚቴው የተናገሩትን በጽሑፍ ገልጸው እንዲያቀርቡ፤ ሁለተኛ፡- “እውነትና ንጋት” በሚል መጽሐፍ መሰል የመዝገብ ቤት ጥራዝ ያነሷቸውን ሐሳቦች በተመሳሳይ መጽሐፍ እንዲያስተባብሉ ትእዛዝ ሰጥቷል፡፡

በጥቅምቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ውሳኔ ለሰባት ዓመት በውዝግብ ከመሩት የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ዋና ሓላፊነታቸው ተነሥተው የትምህርትና ማሠልጠኛ መምሪያ ሓላፊ ኾነው በመሥራት ላይ የሚገኙት ቆሞስ አባ ሠረቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤል ይህን የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ውሳኔ በተግባር ተፈጻሚ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡ ይህን እስካላደረጉ ድረስ ግን በእርሳቸው ላይ የተነሡት ጥያቄዎችና ጥርጣሬዎች አብረዋቸው ይቆያሉ ማለት ነው፡፡

ቆሞስ አባ ሠረቀ ብርሃን በምስክርነታቸው የጠቀሱት፣ የእነ ቀሲስ አስተርኣየ ጽጌንና የአባ ጳውሎስን የነገረ መለኰት ዶክትሬት ዲግሪ ማሟያ ጥናት የሚያስተባብለውና በቅዱስ ሲኖዶስ ፈቃድ ሰባት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትና 11 ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ያዘጋጁት መጽሐፍ ቤተ ክርስቲያናችን በእመቤታችን ክብር፣ ንጽሕናና ቅድስና ስላላት የእምነት አቋም የሚከተለውን ይላል፡- “ቤተ ክርስቲያናችን የምታምነውና የምታስተምረው፡- አምላክን በድንግልና ፀንሳ በድንግልና የወለደች እመቤታችን ድንግል ማርያም ከአዳም ዘር የተላለፈ ኃጢአት (ጥንተ አብሶ) ያላገኛት፣ መርገመ ሥጋ፣ መርገመ ነፍስ የሌለባት፣ ገና ከመወለዷ አስቀድሞ በአምላክ ኅሊና ታስባ ትኖር የነበረች፣ በሰው ልማድና ጠባይ ከሚደርሰው ሥጋዊ ሐሳብና ፈቃድ ሁሉ የተጠበቀች፣ ከተለዩ የተለየች ንጽሕት ቅድስተ ቅዱሳን ናት፡፡”

የአዲስ አበባ 131 ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት 12 አመራር አባላት የወቅቱ የተሐድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴን አስመልክቶ ባቀረቡት 41 ገጽ ሰነድ ጥቆማ ከቀረበባቸው 67 ግለሰቦች መካከል በአጣሪ ኮሚቴው ተጠርተውና ተጠይቀው ለምልአተ ጉባኤው የውሳኔ ሐሳብ የቀረበባቸው ሊቀ ካህናት ጌታቸው ዶኒ ብቻ ናቸው፡፡ በማስረጃው ገጽ 20 ላይ የተሐድሶ መናፍቃን ኑፋቄ አራማጅ ናቸው በሚል ከተዘረዘሩት ግለሰቦች ውስጥ በተ.ቁ ዘጠኝ ላይ የሚገኙት ሊቀ ካህናት ጌታቸው ዶኒ፡- “ለኢትዮጵያ ወንጌላዊት መካነ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን. . .የእናንተ እምነት አስተማሪ በመኾን ተከታይ ለመኾን ባቀረብኹት ጥያቄ መሠረት በአባልነት ተመዝግቤ በመሳተፍ ላይ እገኛለኹ፤. . .” በሚል ቀን ባልተገለጸበት ነገር ግን ፊርማና ቲተራቸው ያለበት ማመልከቻ በሰነድ ማስረጃነት ቀርቦባቸዋል፡፡
በሌላ በኩል በቁ/ል/መ/ፈ/አ/9/2000 በቀን 14/01/2000 ዓ.ም በአቶ ብርሃነ ደሬሳ ከንቲባነት ይመራ ለነበረው የአዲስ አበባ ከተማ ባለአደራ ጊዜያዊ አስተዳደር በጻፉት ፊርማና ቲተራቸውን በያዘ ደብዳቤ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በቀበሌ 02/04 እየተንቀሳቀሰ ለሚገኘው የቅን ልቡና መንፈሳዊ ፈውስ አገልግሎት የእምነት ተቋም ሕገ መንግሥት በሰጠው መብት እንደ ማንኛውም አገር በቀል የእምነት ተቋም ከፍትሕ ሚኒስቴር ሕጋዊ የሰውነት መብት አግኝቶና ተመዝግቦ ያለ የእምነት ተቋም ነው፤” ሲሉ ጽፈዋል፡፡ በቁጥር 11/6361/ፈ/3076 በቀን 10/08/99 ዓ.ም ለፍትሕ ሚኒስቴር በተጻፈ ደብዳቤ “የቅን ልቡና መንፈሳዊ ፈውስ አገልግሎት” እንደ አንድ አገር በቀል ማኅበር ሕጋዊ ሰውነት አግኝቶ እንዲንቀሳቀስ የተጠየቀበት ማመልከቻ ከማስረጃው ጋራ የተያያዘ ሲኾን በቀን 02/11/99 ዓ.ም ደግሞ የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ አብያተ ክርስቲያን በአንድነት በወረዳው ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ተሰብስበው ሊቀ ካህናት ጌታቸው የቤተ ክርስቲያኒቱን ሕግና ሥርዐት በመጣስ እየተንቀሳቀሱ በመኾኑ ክትትል እንዲደረግባቸው ለመንበረ ፓትርያርክና ለሚመለከተው ሁሉ የጻፉት ስም ዝርዝርና ፊርማ ያለበት ጽሑፍ ለአጣሪ ኮሚቴው በማስረጃነት ቀርቧል፡፡
ማስረጃዎቹ ለሊቀ ካህናት ጌታቸው ዶኒ ከተነበቡላቸው በኋላ ሲመልሱ “ለኢትዮጵያ ወንጌላዊት መካነ ኢየሱስ” ተጻፈ የተባለው ደብዳቤ “የእኔ አይደለም፤ ወደዚህ የእምነት ተቋም የመግባቱም ፍላጎት የለኝም፤ አስፈላጊም ከኾነ በፎረንሲክ ይመርመር” በማለት ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡
“የቅን ልቡና መንፈሳዊ ፈውስ አገልግሎት የእምነት ተቋም” በማቋቋም ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያንን በመጣስ ስለ መንቀሳቀሳቸው ሲጠየቁም “በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በደረሰብኝ የአስተዳደር በደልና ችግር ምክንያት የቅን ልቦና መንፈሳዊ የፈውስ አገልግሎት የእምነት ተቋም በማለት ከፍትሕ ሚኒስቴር አስፈቅጄ ስንቀሳቀስ መቆየቴ ግልጽ ነው፡፡ ይህን ስሠራ ከኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክን የተለየ ትምህርት አላስተማርኹም፤ ጽሑፍ አልጻፍኹም፤ ድርጅቱን ያቋቋምኹበት ምክንያት ከቋሚ ሥራዬ ስፈናቀል ለቤተሰቦቼ የማበላው ዳቦ ስላጣኹ ሃይማኖቴንና ክህነቴን ጠብቄ መንፈሳዊ የፈውስ አገልግሎት ስሰጥ ቆይቻለኹ፤ በመጨረሻም ይቅርታ እንዲደረግልኝ ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አመልክቼ ይቅርታ ከተደረገልኝ በኋላ የቅን ልቡና የመንፈሳዊ ፈውስ አገልግሎት የእምነት ተቋም የሚለውን ፈቃድ መልሼ በቤተ ክርስቲያኔ በተለያየ የሥራ ዘርፍ ተመድቤ እያገለገልኹ እገኛለኹ” በማለት ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡ ይቅርታ ተደርጎላቸው በሥራ የተመደቡ መኾኑን የሚያስረዳ ደብዳቤም አቅርበዋል፡፡
የአጣሪ ኮሚቴው ዐቢይ ጉባኤ ሊቀ ካህናት ጌታቸው ዶኒ ‹ለወንጌላዊት መካነ ኢየሱስ› ጻፉት የተባለውን ስምና ቲተራቸውን የያዘ ደብዳቤ እርሳቸው የጻፉት አለመኾኑን የመሰከሩት ቃል ወደፊት መጣራት እንደሚያስፈልገው በማመን አልፎታል፡፡ አቋቁመውት የነበረውን ድርጅት ፈቃድ መልሰው ይቅርታ ተደርጎላቸው በቤተ ክርስቲያናችን ሥራ መመደባቸውን ደግሞ ተቀብሎታል፡፡
ይህን የአጣሪ ኮሚቴውን ዐቢይ ጉባኤ የውሳኔ ሐሳብ የመረመረው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በሊቀ ካህናት ጌታቸው ዶኒ ላይ ባለሁለት ነጥብ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡ በዚህም መሠረት አንደኛ፡- ሊቀ ካህናት ጌታቸው ለ“ኢትዮጵያ ወንጌላዊት መካነ ኢየሱስ” የእምነታቸው አስተማሪ ለመኾን አባል ለመኾን እንደሚፈልጉ የተጠየቀበትን ማመልከቻ እርሳቸው እንዳልጻፉትና የዚህም ፍላጎት እንደሌላቸው ለአጣሪ ኮሚቴው የተናገሩትን ቃል በጽሑፍ እንዲገልጹ፤ ሁለተኛ፡- “የቅን ልቡና መንፈሳዊ ፈውስ አገልግሎት የእምነት ተቋም” በሚል ስላቋቋሙት ድርጅት ይቅርታ የጠየቁ በመኾኑ ቀኖና እንዲሰጣቸው ወስኗል፡፡
ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ በዘንድሮው የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ መደበኛ ስብሰባ መክፈቻ ጸሎት ወቅት በሰጡት የጉባኤው ትኩረት አመላካች ትምህርት ላይ እንደዘገብነው÷ ቅዱስ ሲኖዶሱ ግንባር ቀደም አጀንዳ ባደረገውና ቀናትን በወሰደው የሃይማኖት ጉዳይ ከ1990 ዓ.ም ወዲህ ዐበይት ውሳኔዎችን ማሳለፉን ተከትሎ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ እንቅስቃሴ አራማጅ ድርጅቶችና ግለሰቦች እንደ ኀይለ ጊዮርጊስ ጥላሁን ካሉት የውስጥ አርበኞቻቸው ጋራ በመኾን መጠነ ሰፊ የስም ማጥፋት ዘመቻዎችና ሌሎችም ዐይነት ጥቃቶችን እንደሚከፍቱ (ግብረ መልስ እንደሚሰጡ) ግምት ወስዷል፡፡ በአሁኑ ወቅት እኒህ ግልጽ የወጡና በውስጥ በኦርቶዶከሳዊ ካባ የሚንቀሳቀሱ አጽራረ ቤተ ክርስቲያን የውሳኔዎችን ተፈጻሚነት ለመቀልበስም ይኹን በብፁዓን አባቶች ላይ ሊያደርሱ የሚችሉትን ቀጥተኛ ጥቃት እነርሱ ራሳቸው በመረጡት መንገድ ለመመከት ብቃቱም ዝግጁነትም እንዳለ በገሃድ እንዲያውቁት ያስፈልጋል፡፡
ይህ እንደተጠበቀ ኾኖ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የሊቃውንት ጉባኤ መምሪያው ግልጽ የወጡ አጽራረ ቤተ ክርስቲያን ባፍም በመጣፍም ሊከፍቱት ለሚችሉት ዘመቻ ብቁና ዙሪያ መለስ ምላሽ ለመስጠት በሚችልበት አኳኋን ድርጁና ዝግጁ እንዲኾን ትኩረት ሰጥቶ ተነጋግሮበታል፡፡ በዚህም መሠረት ሊቃውንት ጉባኤው በተጨማሪ የሰው ኀይልና በልዩ በጀት ተጠናክሮ በምልአተ ጉባኤው ውሳኔ እንደተገለጸው እስከ ዛሬ ለተጻፉት የኑፋቄ ሥራዎች ምላሽ እንዲሰጥ፣ በተከታታይ ለሚመጣውም ምላሽ እያዘጋጀ እንዲቀጥል ቅዱስ ሲኖዶሱ ወስኗል፡፡
ምልአተ ጉባኤው ሃይማኖታዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ በፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ አራማጅ ድርጅቶችና ግለሰቦች ላይ ያሳለፈው ውሳኔ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር በሚገኝበት ሁሉና በመላው ዓለም ላሉ ኦርቶዶክሳውያን በሚረዱበት ቋንቋ ተዘጋጅቶ እንዲሰራጭ ለማድረግ ጥንቃቄ የተሞላበት ርምጃ ወስዷል፡፡ ይህም ከወትሮው በተለየ አኳኋን የምልአተ ጉባኤውን ቃለ ጉባኤ በሚይዙ የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ሠራተኞች ሳይኾን በራሳቸው በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ እንዲዘጋጅ መወሰኑ ነው፡፡
በዚህም መሠረት የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ በአጀንዳ ተ.ቁ (13) “ስለ ሃይማኖት ሕጸጽ በኮሚቴው የሚቀርበውን ሪፖርት መስማትና መወሰን” በሚለው ርእሰ ጉዳይ ላይ በመነጋገር ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች በጽሑፍ አዘጋጅተው እንዲያቀርቡ አራት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የሚገኙበትን ኮሚቴ ሠይሟል፡፡ እነርሱም፡- 1)ብፁዕ አቡነ ገሪማ፣ 2)ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ፣ 3)ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል እና 4)ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ ናቸው፡፡
በትናንቱ ከቀትር በኋላ የቅዱስ ሲኖዶስ መደበኛ ስብሰባ በርእሰ መንበሩ አቡነ ጳውሎስ አመራር ላይ የታየው ለውጥ በብዙዎቹ የምልአተ ጉባኤው አባላት ላይ ያሳደረው ስሜት ሳይገለጽ የሚታለፍ እንዳልኾነ የስብሰባው ምንጮች ይጠቁማሉ፡፡ ይህም ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ የግለሰቦቹ ኑፋቄ አንድ በአንድ እየተነበበ የውሳኔ ሐሳቡ ላይ ውይይት በሚካሄድበት ወቅት ከቀትር በፊትና ሰሞኑን ከያዙት ዝንባሌ በተለየ ኹኔታ እየቀደሙ የውግዘት ሐሳብ አቅራቢ መኾናቸው ነው፡፡
ደጀ ሰላም እምነት ይህ ቆይቶ እውንነቱ የሚረጋገጥ የዝንባሌ ለውጥ ከመጀመሪያው የስብሰባው ቀን አንሥቶ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ በማዘናጊያ አጀንዳዎች ብዙም ሳይጠመዱ ርእሰ ጉዳያቸውን ለይተው በማወቅ በንቃትና በአንድነት ተግባብተው በመወያየት የነበራቸው የተዋሐደ ጥረት ውጤት ነው፡፡ በዚህም ድሉ ለቀናዒ ኦርቶዶክሳውያን አገልጋዮችና ምእመናን ሁሉ ነው፡፡ በተለይም የየራሳቸውን ድርሻ በመወጣት ለዚህ ውጤት መገኘት ቀጥተኛ አስተዋጽኦ የነበራቸው የየአህጉረ ስብከት አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ሰበካ ጉባኤያትና ሰንበት ት/ቤቶች፣ በበጎ ፈቃድ የተሰባሰቡ የፀረ - ተሐድሶ ሰባክያን ጥምረት፣ የጥምቀት ልጆች አንድነት እንዲሁም የማኅበረ ቅዱሳን አመራርና አባላት መንፈሳዊ ጥብአት ነው፡፡
ደጀ ሰላም የብፁዓን አባቶቻችንን ጉባኤ የቅዱሳን ሐዋርያትና የሠለስቱ ምእት ጉባኤ በማድረግ እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ በማድረግ ለዚህ አንጸባራቂ ውሳኔ ያበቃውን ልዑል እግዚአብሔር ታመሰግናለች፡፡ ለብፁዓን አባቶቻችን ሰላምን፣ ረጅም ዕድሜንና ጤናን ከደገኛ አገልግሎታቸው ጋራ እንዲሰጣቸው፣ በሌሎቹም የቤተ ክርስቲያን አንገብጋቢ ጉዳዮች ተመሳሳይ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ልባዊ መሻቷን በፊቱ ታቀርባለች፡፡ በየመዋቅሩና በየሥፍራው ለሚገኙ ለፀረ - ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ አደረጃጀቶች ሁሉ ስኬቱ የእናንተ ነው፤ እንኳን ደስ አላችኹ!! ውሳኔው በየአካባቢያችን ያለውን ተፈጻሚነትም በንቃትና በቀጣይነት እንከታተለው በማለት መልእክቷል ታስተላልፋለች፡፡
ይትባረክ እግዚአብሔር አምላከ አበዊነ!!
ቸር ወሬ ያሰማን፤
አሜን፡፡

0 comments:

Post a Comment