Thursday, February 26, 2015

ተመየጢ ተመየጢ ሱላማጢስ

    በስመ ስላሴ!

Add caption
አንቺ ሱላማጢስ ሆይ፥ ተመለሽ፥ ተመለሽ እናይሽ ዘንድ ተመለሽ፥ ተመለሽ። መኃልይ 7፤ 1
አንቺ ሱላማጢስ አንቺ ሰላማዊት…ነቢያት የሰላም አለቃ ያሉትን ሰላማዊ ኢየሱስ ክርስቶስን የወለድሽልን ኢሳይያስ (9፡6) ድንግል ማርያም ሆይ ተመለሺ ተመለሺ...
ጌታ ልቡ ያሀነና የተከዘ አዳምን ያድነው ዘንድ በወደደ ጊዜ የመዳን ምልክት የህይወት መሰላል እንድትሆኝ የመረጠሽ ሱላማጢስ ሆይ ሰላማዊት እመቤት ድንግል ማርያም ሆይ ልቤ የህይወትን ውሃ ተጠምቶዋልና ወደ ልቤ ተመለሺ…(ውዳሴ ማርያም ዘሰኑይ)
የሚበላውን የህይወት መብል የሚጠጣውን የህይወት መጠጥ የወለድሽልን የወርቅ መሶብ ሱላማጢስ ሆይ ሰላማዊት እመቤት ድንግል ማርያም ሆይ ምልጃሽ ካልደገፈኝ ስምሽ ጉልበት ካልሆነኝ ዳገቱን መውጣት ወጥመዱን ማለፍ አልችልምና ወደ ልቤ ተመለሺ…(ዮሐ 6፡51)
የዶኪማስን ቤት ባዶ ማድጋዎች በወይን የመላ ንጉስ ክርስቶስን የወለድሽልን…ባዶ ማድጋዎችን በምልጃሽ መሙላት የምታውቂበት የዶኪማስን የልቡን ጭንቀት የቤቱን ጉድለት ሳትጠይቂ የምታውቂ ከልጅሽ ከወዳጅሽ አማልደሽ ሙላት የምትሆኝ ሱላማጢስ ሆይ  አንቺ ሰላማዊት እመቤት ሆይ የህይወት ወይን ኢየሱስ ክርስቶስን ተጠምቻለሁና ወደ ልቤ ተመለሺ…(ዮሐ 2፡1-11)
የአለም ብርሃን ፀሀየ ጽድቅ ኢየሱስ ክርስቶስን የወለድሽልን እውነተኛውን ብርሃን ለአለም የሰጠን ብርሃን ዘበአማን ዘያበርህ ለኩሉ ሰብእ(ለሰው ልጆች ሁሉ በእውነት ብርሃንን ያበራ ) ተብሎ የተወደሰን ንጉስ ክርስቶስን ያስገኘሽልን አማናዊቷ ምስራቅ የፀሀይ መውጫ ሰላማዊት እመቤት ወላዲተ ብርሃን ድንግል ማርያም ሆይ አንቺ ሰላማዊት እመቤት ሆይ የኃጢአት ጨለማ ውጦኛል ደክሜአለሁ ህይወቴ ያላንቺና ያለ ልጅሽ ብርቱ ጨለማ ናትና ወደ ልቤ ተመለሺ...(ዮሐ8፡12፤ ዮሐ 9፡6፤ ውዳሴ ማርያም ዘሰኑይ  )

ሰላማዊት እመቤት የበደሌ ሸክም በዝቶ ውስጤ እየደማ በኃጢአት አረንቋ ወድቄ አኔ ባርያሽ አየተሰቃየሁ ነው አዛኝቷ እመቤት ሆይ ከሊባኖስ ከዚያ ተራራ ወደደካማው ልቤ ከልጅሽ ጋር ነይልኝ ሱላማጢስ ሆይ ለቀደሙት አባቶች ነለ ቅዱስ አባ ህርያቆስ ለነ ቅዱስ ኤፍሬም የህይወታቸው ጣዕም የቅኔያቸው ምስጢር እንደሆንሽላቸው ለኔም ለደካማው ልጅሽ በእውነት ያለ ሀሰት በእምነት ያለ ጥርጥር ወደ ፍቅርሽ ወደ ደጅሽ ወደ ሰላምሽ ወደ እቅፍሽ መልሺኝ ሱላማጢስ ሆይ ተመለሺ በኃጢአት ወደረከሰው ልቤ ተመለሺ…ተመለሺ ተመለሺ ሱላማጢስ…ተመየጢ ተመየጢ ሱላማጢስ…
                           
             

             የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ልመናዋ ፍቅሯ እናትነቷ ለዘለኣለሙ በእኛ ጸንቶ ይኑር አሜን!

0 comments:

Post a Comment